ኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ በኢኮኖሚው መስክ ትብብራቸውን ያጠናክራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ በኢኮኖሚው መስክ ትብብራቸውን ያጠናክራሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የፊስካል ጉዳዮች የስራ ዘርፍ ጋር የሥራ ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ በዋናነት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ለመደገፍ በሚሰጡ የቴክኒክ ድጋፎች ላይ ያተኮረ ነው።
የመንግሥት የፋይናንስ አሠራርና የበጀት አጠቃቀም ግልጽነትን ማሻሻል እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶችን ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕቅድና በጀት ጋር ማጣጣም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክሯል።
የታክስ ፖሊሲና አስተዳደርን በተመለከተ፣ የኢትዮጵያን የታክስ ሥርዓት ለማዘመን፣ የታክስ መሠረቱን ለማስፋት እንዲሁም በዲጂታላይዜሽንና በተቋማዊ አቅም ግንባታ አማካኝነት የታክስ ሕግ ተገዢነትን ለማሻሻል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁለቱ ወገኖች ተወያይተዋል።
የአይኤምኤፍ ቡድንም ኢትዮጵያ ፍትሃዊነትንና ቀልጣፋ የታክስ ሥርዓትን በማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው የገቢ ዕድገት እንድታስመዘግብ የታለመ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጧል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች (SOE) ሪፎርምን በተመለከተ፣ ልዑኩ መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከር እንዲሁም የዋና ዋና የልማት ድርጅቶችን አፈጻጸምና ተጠያቂነት ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ቀጣይነት ያለው ጥረት አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።
አይኤምኤፍ በበኩሉ የተጀመሩ ጥረቶችን በማበረታታት፣ የፊስካል ስጋቶችን ለመቀነስ ጠንካራ የክትትል ማዕቀፎችና ግልጽ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓቶች ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥቷል።
በፊስካል ግልጽነት ዙሪያ የተደረገው ውይይት የሕዝብ ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የበጀት ተዓማኒነትን ማሻሻልና የፊስካል ሪፖርቶችን ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር ማጣጣም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
የኢትዮጵያ ልዑክም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን የሪፎርም አጀንዳ ዋና ምሰሶ መሆኑን በመግለጽ የመንግሥትን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በሚሰጡ የቴክኒክ ድጋፎች ላይ፤ አይኤምኤፍ መንግሥት የአየር ንብረት ፖሊሲዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም የሚያደርገውን ጥረት እየደገፈ መሆኑ ተገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች የቴክኒክ ግንኙነቱን ለማሳደግና የኢትዮጵያ ሪፎርም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለመደገፍ በቅርበት ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
የኢትዮጵያ ልዑክ አይኤምኤፍ (IMF) ላሳየው ቀጣይነት ያለው አጋርነት፣ ለአቅም ግንባታና ለተቋማዊ ጥንካሬ ለሚያደርገው ድጋፍ ያለውን አድናቆት መግለጹን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።