ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ያላትን ልምድ ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አጋራች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ያላትን ልምድ ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አጋራች
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ ያካበተችውን ተጨባጭ ልምድ ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባላት አጋርታለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የመሩትን የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሚኒስትሮች ስብሰባን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሊቀ መንበርነት ሚናዋን በብቃት እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በበይነ-መረብ በተካሄደው በዚህ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮ ለማጋራት አመቺ ዕድል መፈጠሩን ቃል አቀባዩ አንስተዋል።
ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለኢኮኖሚ፣ ለአስተዳደር እንዲሁም ለሰላምና ፀጥታ ሥራ ያለውን የጎላ ፋይዳ ለሚኒስትሮቹ አስገንዝበዋል ብለዋል።
በተለይም ቴክኖሎጂው ግጭቶችን በመከላከል፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን በማስተላለፍ እና የሰላም ሂደቶችን በመደገፍ ረገድ ያለውን አበርክቶ አብራርተዋል።
አምባሳደር ነብያት አክለውም፣ በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቅንጦት ሳይሆን ጠቃሚ የልማት መሣሪያ መሆኑን ኢትዮጵያ ተገንዝባለች ብለዋል።
በዚህ ዘርፍም የተቀናጁ ተቋማትን በማቋቋም ህዝቡ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ቀልጣፋ ዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተሞክሮ እና በአቅም ግንባታ ረገድ እየተከናወነ ያለውን የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ በአብነት ለመድረኩ መቅረቡን ተናግረዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሻምፒዮን ሆነው መመረጣቸው፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት እንድታካፍል ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
አፍሪካ በቀደመው የኢንተርኔት ዘመን ዘግይታ መግባቷን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ አሁን ግን አህጉሪቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘመን ተገቢውን ቦታ በመያዝ የመሪነት ሚና እንዲኖራት ኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ አቋም በመድረኩ ማንጸባረቋን ገልጸዋል።