ባለፉት ዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ “ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትና የተሳለጠ የገበያ ትስስር ለኢኮኖሚ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የተቋሙ ተልዕኮ የመፈጸም አቅሙ በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በዘጠኝ ወራቱ በኦንላይን ንግድ ምዝገባ፣ አዲስ ፈቃድ የማውጣት፣ የማደስ እና መሰረዝ ሥራዎች ለሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በወጪ ንግድ ረገድ ከሁሉም የንግድ ዓይነቶች ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል።
የገበያ መሠረተ ልማትን በማስፋት ረገድ ገበያን ለማረጋጋት የሚረዱ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 2ሺህ 190 መድረሱን ተናግረዋል።
ሁለተኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላትን የማስፋት ስራ መጠናከሩን አንስተው፤ በዘጠኝ ወራት ሁለት ማዕከላት ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ሌሎች ሰባት ማዕከላት በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በምርት ጥራትና ቁጥጥር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልፀው፤ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚመጥኑ ደረጃዎችን የማውጣትና የማስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ተናግረዋል።
የንግድ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለተገልጋዩ ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ስራ በስፋት ተከናውኗል ብለዋል።
ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠርና ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት፤ ሀገራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ሥርዓት ላይ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፋብሪካን ጨምሮ ወደ ገበያውን የሚገቡ ምርቶችን በመፈተሽና የቀረቡ ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ ረገድም ውጤታማ ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።