የመደመር ዕሳቤ ውጤት የሆነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለአካባቢው የብልፅግና ተስፋን ይዞ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር ዕሳቤ ውጤት የሆነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለአካባቢው የብልፅግና ተስፋን ይዞ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የመደመር ዕሳቤ ውጤት የሆነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለአካባቢው የብልፅግና ተስፋን ይዞ መጥቷል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ"ገበታ ለትውልድ" ኢኒሼቲቭ ተገንብቶ የተመረቀው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ የመደመር ዕሳቤ ውጤትና ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ ህልሞቻቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ማሳያ ነው።
ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ላገዙ የፀጥታ ኃይሎች፣ የአካባቢው አመራሮችና ለሕዝቡ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ላሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር ከፍተኛ አድናቆት ሰጥተዋል።
አቶ በላይነህ በሪዞርቱ ቅጥር ግቢ የነበረውን ጫት በሙዝ፣ በፓፓያና በቡና መተካታቸውና ለአካባቢው አርሶ አደሮችም የሙዝ ችግኝ በነጻ ማከፋፈላቸው ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሎ የኢትዮጵያ የአንድነትና የብዝኃነት ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው፤ "ወሎ ማለት ኅብር ማለት ነው፤ ታሪኩ፣ ባህሉ፣ እምነቱ፣ ቋንቋው፣ ዜማው፣ ገበያው፣ መልክአ ምድሩ ኅብር ነው" ብለዋል።
ሪዞርቱ ከአንኮበር፣ ላሊበላ፣ አክሱም እና ኤርታሌ ለሚጓዙ ቱሪስቶች እንደ ስበት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ ሌሎች ባለሀብቶችም መሰል የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አካባቢው በግብርና ምርታማነት ሊለወጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከቆቦ እስከ መካነ ሰላም እንዲሁም ከዋግ እስከ አጣዬ ለም መሬትና የውኃ ጸጋ መኖሩን ጠቅሰው፤ አካባቢው ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት መሸጋገር እንዳለበት አሳስበዋል።
ተግተን ከሠራንና ፀጋዎቻችንን ካለማን የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ጉዞን እናሳካለን ብለዋል።
የልማት ውጤቶች የተመዘገቡት ሰላም በመኖሩ መሆኑን በመጥቀስ፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን አጥብቀው እንዲጠብቁ አደራ ብለዋል።
እንዲሁም መጭው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።