የሳዑዲ የልማት ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር አጋርነቱን ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋገጠ - ኢዜአ አማርኛ
የሳዑዲ የልማት ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር አጋርነቱን ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋገጠ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8/2018(ኢዜአ)፦ የሳዑዲ የልማት ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኝነቱን ገለጸ።
ዓመታዊው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ የፀደይ ወቅት ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ መካሄዱን ቀጥሏል።
በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ፣ ከስብስባው ጎን ለጎን ከሳዑዲ የልማት ፈንድ (SDF) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱልጣን አብዱልራህማን አል-ማርሻድ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርጓል።
በስብሰባው ወቅት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ያለውን ጠንካራ እና እያደገ የመጣ አጋርነት አድንቀዋል።
ሚኒስትሩ የመንግሥትን ቀጣይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ በአጽንኦት ያነሱ ሲሆን፣ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ የሚሹ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የኢንቨስትመንት ዘርፎችም አብራርተዋል።
ለስትራቴጂካዊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ በተለይም ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሊቀርብ የሚችል ፋይናንስን እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገት እና ቀጣናዊ ትስስርን ለመደገፍ የሚደረገውን የመንገድ ትስስር ማስፋፊያን ያካተቱ ሀሳቦች በውይይቱ ላይ ተነስተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች ስኬታማነት ቀጣይነት ያለው ትብብር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ሱልጣን አብዱልራህማን አል-ማርሻድ በበኩላቸው የሳዑዲ የልማት ፈንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ቁልፍ የሆኑ የኢትዮጵያ የልማት ኢኒሼቲቮች ለመደገፍ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።