በክልሉ የፍትህ ስርዓቱን ፈጣን፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፍትህ ስርዓቱን ፈጣን፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ናቸው
ባህርዳር ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የፍትህ ስርዓቱን ፈጣን፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑን የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ገለጸ።
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ስራ አስፈፃሚ አባላትና አመራሮች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ክንውንና አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚሁ ጊዜ አስተያየታቸውን የሰጡት የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ህብረት አቡሃይ፤ በክልሉ የፍትህ ስርአቱን በማሻሻልና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አይተናል ብለዋል።
የሪፎርም ስራው ጅምር ትልቅ ለውጥ የታየበት መሆኑን አንስተው እስከ ታች በማውረድ የዜጎችን የፍትህ ፍላጎትና ተደራሽነት ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የፍትህ ስርዓቱን ፈጣን፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑን አንስተው በተለይም የሴቶችና ህፃናት የፍትህ አገልግሎት በልዩ ትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠሉ እንዳለ ሆኖ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ይበልጥ መስራት እንደሚገባም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፤ የፍትህ ስርዓቱ ሪፎርም አገልግሎቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የባህል ፍርድ ቤቶች በህግ ዕውቅና አግኝተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው በሁሉም ረገድ ዜጎች ፈጣንና ሚዛናዊ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም በሪፎርሙ የሚታዩ ለውጦችና ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተው በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።