ጥምረቱ ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የምታከናውናቸውን ውጤታማ ተግባራት መደገፉን ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ጥምረቱ ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የምታከናውናቸውን ውጤታማ ተግባራት መደገፉን ይቀጥላል
ሀዋሳ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን ለማረጋገጥ የምታከናውናቸው ውጤታማ ተግባራት መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) ገለጸ።
የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ-AGRA) ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በሲዳማ ክልል የኤልቶ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን የሥራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።
አግራ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮችን በግብዓትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ግብርናን ለማሳደግ እኤአ በ2006 የተመሰረተ አፍሪካ መር ተቋም ነው።
አግራ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ አተኩሮ የሚሰራ ሲሆን የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የአፈር ለምነት ማስጠበቅ፣ የገበያ ትስስርን ማመቻቸትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግቦችን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ያለ ጥምረት ነው።
የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጥምረቱ የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ ጥምረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በ16 ሀገራት የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍ ያደርጋል።
በተለይም በኢትዮጵያ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተለያየ መንገድ እየደገፈ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የጥምረቱ ፕሬዚዳንት አሊስ ሩህዌዛ በበኩላቸው ድርጅቱ በአፍሪካ የግብርና ስርዓት ሽግግርን ለማጠናከር በተለይም አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ነው ብለዋል።
አግራ አርሶ አደሮች ባላቸው አነስተኛ ማሳ ላይ አስፈላጊው ግብዓትና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያምናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህም የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፋጠን ያደርጋል፤ ውጤትም ታይቶበታል ብለዋል።
በአግራ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ይኼነው ዘውዴ (ዶ/ር) ጥምረቱ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓትን ከማሳለጥ ባሻገር የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የማድረግ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ለማረጋገጥ የማገዝ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር የተከናወኑ ግብርናን የማዘመን፣ ምርታማነትን የማረጋገጥና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማሳደግ ጥረቶች ውጤት ማስመዝገባቸውን አንስተዋል።
የሲዳማ ኤልቶ የገበሬዎች የህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ዮሐንስ ጥምረቱ በፈጠረው የተቀናጀ ስራ አባላቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም የቴክኖሎጂ አቅርቦቱ የሚጠፋውን ጊዜና ጉልበት በማዳን፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያውን የማረጋጋት ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።