ቀጥታ፡

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በአካባቢው ያለውን ልማት በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ ነው 

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በአካባቢው ያለውን ልማት በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም መመረቁ ይታወቃል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሐይቅ ከተማ በመገኘት የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን ዛሬ ሥራ አስጀምረዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ወደ ተጨባጭ ልማት በመቀየር ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳቦች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ርብርብ ለውጤት የበቃ፤ በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መንግሥትና ተቋራጮች በጋራ በመሆን ያሳኩት፤ ሕዝብን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ላለን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ወሎ የበርካታ ኃይማኖታዊ እና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች መገኛ ናት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ወደ ሥራ መግባት ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው ለሚሰሩ ሌሎች ልማቶችም ምሳሌ እንደሚሆን ጠቁመው፤ ልማቱን በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው፤ ለውጡን ተከትሎ ልማቱ በሁሉም አካባቢዎች እንዲዳረስ መንግሥት የቀየሰው ሥልት ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መስኮች ዘመናትን የተሻገረ መስተጋብርና ትስስር ያላቸው መሆኑንም አንስተዋል።

በአማራ ክልል እየተመዘገበ ያለው ልማት በዘላቂነት ሕዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሰላም ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም በክልሉ ያለው አመራር፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች በጋራ መሥራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

የአፋር ክልልም በሰላም ዙሪያ ከአማራ ክልል ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው፤ በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ግንባታ ተሳትፈን የታሪክ ተካፋይ የመሆን ዕድል በማግኘታችን ጥልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።


 

በተለያዩ አካባቢዎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በሰፊው እየተሳተፍን ነው ያሉት አቶ በላይነህ፤ በቀጣይም በልማት ዙሪያ ከመንግሥት ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

በትብብር መሥራት ከተቻለ የማይሳካ ነገር እንደሌለ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም