ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ግብ ለማሳካት የዲጂታል አስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ግብ ለማሳካት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ክህሎትና የዲጂታል አስተሳሰብ ለውጥ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በለጠ እሱባለው ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ከአፍሪካ ዲጂታልና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ጋር በመተባበር "አመራር በሰው ሰራሽ አስተውሎት" በሚል መሪ ሃሳብ ሴሚናር አዘጋጅቷል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በለጠ እሱባለው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን መገልገል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ሆኗል፡፡

ዘመኑ የሚጠይቀውን አመራር ለመስጠት በዘርፉ ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸው፤ እንደ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ያሉ ተቋማት ደግሞ ሥራቸው ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ፓርኩ በዘርፉ ልምድና አቅም ያላቸው ባለሙያዎችን በማምጣት የተቋሙን ሰራተኞችና የሥራ ሀላፊዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ግንዛቤ እንዲፈጠርላቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን የተቋሙን ግብ ለማሳካት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን መሰረት ያደረገ ጥረት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያን 2030 ስትራቴጂ ግብ ለማሳካት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ክህሎትና የዲጂታል አስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ዲጂታልና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ቦርድ ሊቀ መንበርና የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ባህሩ ዘይኑ፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ በመረዳት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አቋቁማለች ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ /ኤ.አይ/ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት በሂደት ላይ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ገዥና ተቀባይ እንደነበረች አስታውሰው፤ ፖሊሲ በማዘጋጀት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ቴክኖሎጂ ሰጭና ለሌሎች ሀገራት አቅራቢ ወደ መሆን ደረጃ ተሸጋግራለች ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ዲጂታልና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ተባባሪ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ሸጋው አናጋው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሁሉም ዘርፎች ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ሰው ሰራሽ አስተውሎት የአሰራር ለውጥ መፍጠሩን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ሸጋው፤ የተቋማት መሪዎች በቀደመው መንገድ መምራት አይችሉም ብለዋል፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ውጤት በሚያመጣ መንገድ ለመጠቀም የተቋማት መሪዎችን በቴክኖሎጂ ማብቃት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር ለማምጣት የአስተሳሰብና የባህል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕውቀትና ክህሎት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ሁኔታዎችን አስቀድሞ በመተንበይ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ አመራር ለመስጠት ክህሎት፣ ሥነ ምግባርና ሽግግር መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡


 

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመሪነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግሥት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ፖሊሲ በማውጣት ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በፍጥነት እያደገ ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዘርፉን እድገት የሚመጥን የመንግስት ቁርጠኝነት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም