በጠቅላላ ምርጫው ለሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው ለሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል
ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለሴቶችና ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶቹ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ለመራጭነት የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱም ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች መካከል ቤዱና ኡከች፤ እየተቃረበ ባለው 7ኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተለይም ለሴቶችና ለወጣቶች ተጠቃሚነት ለሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ለዚህም ለመራጭነት የሚያበቃትን ካርድ መውሰዷንና ሌሎች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶችም ካርድ እንዲወስዱ እየቀሰቀሰች መሆኗን ጨምራ ገልፃለች።
ለሴቶችና ወጣቶች መብትና ጥቅም የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቷን የተናገረችው ደግሞ ወጣት ኛጆክ ኮንግ ናት።
በምትኖርበት ቀበሌ ወጣቶችና ሴቶች የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይጠቅመኛል የሚሉትን ፓርቲ እንዲመርጡ እየሰራች መሆኗንም ገልፃለች።
ወጣት ካሰች ታፈሰ በበኩሏ፤ዴሞክራሲያዊ መብቷን ተጠቅማ ይበጀኛል የምትለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ቀደም ብላ ለመራጭነት የሚያበቃትን ካርድ ወስዳለች።
በምርጫውም ለሴቶችና ወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይሰራል ለምትለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጿን ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግራለች።