ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ነው

መተማ ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ከተማ አስተዳደሩ የማህበረሰቡ ቁልፍ ጥያቄ የሆነውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ 

የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት በማህበር ተደራጅተው ሲቆጥቡ ለነበሩና መስፈርቱን ላሟሉ 580 ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ዛሬ ሰጥቷል፡፡

የጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ አቶ ታረቀኝ አለማየሁ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩ የማህበረሰቡ ቁልፍ ጥያቄ የሆነውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።


 

በዚህም በ32 ማህበራት በመደራጀት ሲቆጥቡ ለነበሩና ሌሎች መስፈርቶችን ላሟሉ 580 ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መስጠቱን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል 9 ነጥብ 3 ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማዘጋጀት ለእያንዳንዱ ሰው 160 ካሬ ሜትር ቦታ ዛሬ ማስረከብ መቻሉን አስረድተዋል። 

ለመሬት ካሳ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ በመክፈል ከ3ኛ ወገን ነጻ በማድረግ ማስረከቡን ጠቁመው እድሜያቸው ለደረሰ የልማት ተነሺ ልጆችም የቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን ተናግረዋል። 

እያንዳንዱ የማህበር አባል በተሰጠው ቦታ ላይ በተሰጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ፈጥኖ ወደ ስራ በመግባትና አካባቢውን በማልማት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል።


 

የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪ አቶ ሽፈራው አለነ፤ የከተማ አስተዳደሩ የቤት መስሪያ ቦታ በመስጠት የዘመናት ጥያቄያቸውን ዛሬ እንደፈታላቸው ገልጸዋል።

በተሰጣቸው ቦታ ላይ ቤት ፈጥነው በመገንባት ሃብት ለመፍጠርና አሁን ካሉበት የቤት ኪራይ ችግር ለመላቀቅ ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ሌላኛው የቤት መስሪያ ቦታ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ አታለለ መርሻ በበኩላቸው፤ የብዙ ጊዜ ችግር የነበረውን የመኖሪያ ቦታ ይሰጠኝ ጥያቄ በመፈታቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። 

መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀው በተሰጣቸው ቦታ ላይ በተባለው ጊዜ ቤት ገንብተው ለማጠናቀቅ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። 

በቦታ ርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የማህበር አባላትና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም