ቀጥታ፡

በክልሉ የህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ባህል እያደገ መጥቷል

ዋጂፎ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ባህል እያደገ መምጣቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ጋሞ ዞን የ2018 ዓ.ም የበልግ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር "አረንጓዴ አሻራ ለተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በምዕራብ አባያ ወረዳ ዋጂፎ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ በዘላቂነት ለመቋቋም ለችግኝ ተከላ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

የለውጡ መንግስት በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰትን ችግር መቋቋም እንዲቻል ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተተከሉ ችግኞች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያገዙ መሆኑን ጠቀመው፣ በክልሉ ህብረተሰቡ ችግኝ የመትከልና አካባቢውን የመንከባከብ ሥራ ባህሉ እያደረገ መምጣቱን ተናግረዋል። 


 

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አደጋ ለመከላከል ችግኝ ተከላን የዘወትር ተግባር ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት አበባየሁ (ዶ/ር)፣ ችግኝ ተከላው ለግብርና ምርታማነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ገቢን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል።

ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የሚከናወነውን የልማት ሥራ ማጠናከር ይገባል ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊና የዲላ ክላስተር አስተባባሪ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ናቸው። 


 

መርሀ ግብሩ ለምግብ ዋስትና፣ ለዘላቂ ልማት፣ ለኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲሁም ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የማይተካ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በመሆኑም ዘንድሮ በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የጠቀሱት መሪሁን (ዶ/ር)፣ ግብርናን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዘንድሮ የበልግ ወቅት በሚከናወን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ትግበራ መገባቱን አንስተዋል።

በተለይ በዞኑ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተፈጥሮን በአግባቡ ባለመንከባከብ የሚከሰቱ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ለችግኝ ተከላው ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።


 

በምዕራብ አባያ ወረዳ የዋጂፎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሃምሳ አለቃ ዋጋሶ ኦቼ እና አቶ ዳንኤል ዳንጋሮ በበኩላቸው ቀደም ሲል በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተተከሉ ችግኞች በአካባቢያቸው ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

በየዓመቱ በተተከሉ ችግኞች ቀደም ሲል ሞቃት የነበረው የአካባቢው የዓየር ጸባይ እየተስተካከለ መምጣቱን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በግብርና ሥራም ተጨባጭ ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በመርሀ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፍራፍሬዎች በማልማት ተጨማሪ ገቢ ከማግኘት ባለፈ፣ ለጓሮ አትክልትና ለእንስሳት መኖ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

ይህን ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሀግብር መሳተፋቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም በችግኝ ተከላና እንክብካቤ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል። 

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ እንዲሁም የከተማ አስተዳደር የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም