በአሶሳ ከተማ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ በክልሉ ሠላምን ለማጽናት ለተከናወኑ ተግባራት እውቅና የሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ ከተማ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ በክልሉ ሠላምን ለማጽናት ለተከናወኑ ተግባራት እውቅና የሰጠ ነው
አሶሳ፤ሚያዝያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦በአሶሳ ከተማ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ በክልሉ ሠላምን ለማጽናት ለተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እውቅና የሰጠ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ እና የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የጉባዔውን ማጠቃለያ አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም መንገሻ በመግለጫቸው ወቅት ለሁለት ቀናት የተካሄደው 7ኛው የሰላም ኮንፈረንስ ክልሉ የሰላምን ዋጋ በመረዳት ላከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ዕውቅና የሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል።
በክልሉ ሰላምን ለማጽናት ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የጉባዔው መዘጋጀት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር የጀመርናቸውን ስራዎች ለማስቀጠል የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በክልሉ ለተገኘው ሰላም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ የሰላም ኮንፈረንሱ በክልሉ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት ለሚያከናውኑት የሰላም ማጽናት ተግባራት ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ጉባዔው የሃይማኖቶች የሰላምና አብሮነት አስተምህሮ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የተከናወኑ ስራዎችን የጉባኤው ተሳታፊዎች በተሞክሮነት የወሰዱት እና ስለ ሰላም የተሰበከበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
8ኛው የሰላም ኮንፍረንስ ከሁለት ወራት በኋላ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገልጸዋል።