ቀጥታ፡

የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ በመውሰድ ተዘጋጅተናል- ነዋሪዎች

ሰቆጣ ፤ሚያዚያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ በመውሰድ ተዘጋጅተናል ሲሉ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ በመውሰድ ተዘጋጅተዋል። 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰቆጣ ወረዳ ባጊሚላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አበራ ዘገዬ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።


 

ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመንግስት ስልጣን የሚያዝበት በመሆኑ ይበጀናል ይጠቅመናል ያልነውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ሁሉም መምረጥ የሚችል ዜጋ የመራጭነት ካርድ ሊያወጣ እንደሚገባ የመከሩት አርሶ አደር አበራ የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን እለት በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሰሃላ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሰርፀ በበኩላቸው፤ የመራጭነት ካርድ በማውጣት የዜግነት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።


 

ካርዱን ለማውጣትም የአካባቢያቸውን ሴቶች በመቀስቀስና አብሮ በመሄድ በጋራ ማውጣታቸውን ጠቁመው በካርዳቸው የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ማውጣታቸውን የገለጹት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሳ አበባው ናቸው።

ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ጠንካራና ሰላማዊ አገር ለመገንባት መሰረት በመሆኑ በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።


 

በቀሪ ቀናትም የምርጫ ካርድ ያላወጣው ነዋሪ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ ተመዝግቦ ካርዱን በእጁ መያዝ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

ግንቦት 24/2018 ዓ/ም ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ እየተካሄደ ያለው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዚያ 14/2018 ዓ/ም መራዘሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም