የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት እያደገና የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት እያደገና የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት እያደገና የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡልልታ ገለጹ።
የተቀናጁ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ምርቶች የሚሰበሰቡባቸው፣ የሚቀነባበሩባቸው፣ የታሸጉ ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡባቸውና ወደ ውጭ ለመላክ የሚዘጋጁባቸው ማዕከላት ናቸው።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት፣ ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ መላክ፣ የግብርና ምርትን ማዘመንና የሥራ ዕድል መፍጠር ከተቋቋሙባቸው ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡልልታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ የገቡት የይርጋለም፣ ቡልቡላ፣ ቡሬ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት እያደገ እና የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ ይገኛል።
ሌሎች የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማዋል ለኢንዱስትሪ እድገት ዋና መሰረት ነው።
አገራት ቀጣይነት ላለው ኢኮኖሚያዊ እድገትና ተወዳዳሪነት እሴት ጨምሮ የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃ ምርቶች መላክ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥና ለውጭ በማቅረብ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ስራ አቁመው የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ በማስገባትና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ማሰቻሉን አንስተዋል።
በየዓመቱ የሚዘጋጀው ሀገር አቀፍ ኤክስፖና ባዛርም ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ደረጃ ከማሳየትና የገበያ ትስስር ከመፍጠር አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።