ቀጥታ፡

የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ለሀገርም ሆነ ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል

ሰመራ፣ሚያዝያ 8/2018 (ኢዜአ)፦የሉሲ ሙዚየም መገንባት ለሀገርም ሆነ ለአፋር ክልል የቱሪዝም እድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ የሉሲ ሙዚየም በሠመራ ከተማ ለመገንባት የፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት በዛሬው ዕለት አድርገዋል።


 

በስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) የለውጡ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመተግበር ላይ ከሚገኙ የኢኮኖሚ አውታሮች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው።

ለዚህም የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባት ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዲያበረክት እያደረገ ነው ብለዋል።

የሉሲ ቅሪት አካል መገኛ በሆነው አፋር ክልል ሙዚየሙን የመገንባት ስራውም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሙዝየሙ ለዘርፉ ተመራማሪዎችና ቱሪስት ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ሙዚየሙ የሰው ልጅ አመጣጥና ዝግመተ ለውጥ የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ የሚካሄድበት ከመሆኑም በተጨማሪ የአፋር ህዝብ ቱባ ባህሎች ለማስተዋወቅ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በወቅቱ የተገኙት የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር በበኩላቸው፥ የሙዚየሙ ግንባታ የክልሉን ብሎም የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያጎላ ነው ብለዋል።

የአፋር ክልል ሉሲን ጨምሮ የበርካታ ቅሪተ አካላት መገኛ መሆኑን ጠቁመው፥ ዘርፉን በሚገባ በማልማት ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ስራዎች ተያይዘው እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።

የሚገነባው ሙዚየም የሀገርን ገፅታ በማሳወቅና ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ በበኩላቸው፥ የክልሉን ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦችን በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጉላት በትኩረት መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪስት ሀብት ለማስተዋወቅ የሚያግዘው የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ስምምነትም ተደማሪ አቅም መሆኑን አንስተዋል።

በአስራ ሰምንት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ክፍት የሚሆነው ፕሮጀክቱ 329 ሚሊየን 873 ሺህ 869 ብር በጀት የተያዘለት መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም