ቀጥታ፡

አዳዲስ አሰራሮችን በመጠቀም ካለማነው የበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን- የተሁለደሬ ወረዳ አርሶ አደሮች

ደሴ፤ሚያዚያ 8/2018 (ኢዜአ)፡- የምርት ማሳደጊያና  አዳዲስ አሰራሮችን በመጠቀም ካለሙት የበጋ መስኖ ስንዴ  የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

በበጋው መስኖ ስንዴ ልማቱ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል  አህመድ መንገሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት ካገኙት ጥቅም ልምድ በመውስድ በዘንድሮው በጋ ስራውን በማሳደግ አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬታቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ አልምተዋል።

ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን በአግባቡ መጠቀማቸውንና ያልተቋረጠ የባለሙያ ድጋፍ በማግኘታቸው  የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ  ገልጸዋል።

ለአጨዳ የደረሰውን የስንዴ ሰብል በጥንቃቄ በመሰብሰብና በመውቃት ከ25 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየጣሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ቀደም ሲል በባህላዊ መስኖ አትክልት ለማልማት ጥረት ብናደርግም ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ያሉት አርሶ አደሩ አሁን ላይ በዘመናዊ መስኖ ስንዴ በማልማታችን ተጠቃሚነታችን አድጓል ብለዋል።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ሁሴን አህመድ በበኩላቸው የዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ አቋም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ በመሆኑ ጥሩ ምርት እንጠብቃለን ሲሉ ገልጸዋል።

በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩትን የስንዴ ሰብል  በመሰብሰብ መሬቱን ለመኸር ሰብል ልማት ለማድረስ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

የታቀደውን ምርት ለማግኘትም ዘመናዊ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

አርሶ አደሩ የደረሰውን ሰብል በፍጥነት በመሰብሰብ ለመጪው መኸር እያደረገ ያለውን የእርሻ ዝግጅት አጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህና  በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የተመራ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ በበጋ መስኖ የለማ ስንዴን መጎብኘቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም