ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል

ሚያዝያ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን  የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

በሸገር ከተማ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን አስመልክቶ የመስክ ምልከታ እየተካሄደ ነው።

በመስክ ምልከታው ላይም የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎ እንደገለፁት፤ በሸገር ከተማ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል። 

ከተማዋ ከተመሰረተች በኋላ እየተከናወኑ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የህብረተሰቡን ህይወት የቀየሩ ከመሆናቸውም በላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን እውን ከማድረግ አኳያ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ከለውጡ በኋላ በከተማዋ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ ዘመናዊ አገልግሎቶችን በማስፈን፣ ክህሎትን በማዳበር እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ ረገድ በተሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን አክለዋል።


 

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመፍታትና አገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን ጎን ለጎን በከተማዋ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በምርምር በመለየት መሰራቱን አመልክተዋል።

የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ ከ1 ሺህ 300 በላይ አርሶ አደሮች ክህሎታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የኢንቨስትመንት እድገቱን ከተማው ከመመስረቱ በፊት ከነበረው በእጥፍ ማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎችን ጨምሮ አጠቃላይ 1 ሺህ 504 ኢንቨስትመንቶች  4 ሺህ 493 ሄክታር መሬትን ማልማት ችለዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም