ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ለአፍታም የሚቆም አይደለም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ለአፍታም የሚቆም አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ኢተያ አካባቢ የተገነባውን የአሠላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱን ክሮግስትራፕን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአርሲና አካባቢው ህዝብ ተግቶ በመስራት የሚታወቅና ትርፍ አምራች አካባቢ ነው ብለዋል።

ስንዴና ገብስን በከፍተኛ መጠንና ጥራት እንደሚያመርት ገልጸው፤በተጨማሪም አካባቢው በነፋስና ጂኦ ተርማል የታዳሽ ኃይል አማራጮች ለኢትዮጵያ የዕድገት አቅም እንዳለው አብራርተዋል።

ከለውጡ በፊት የነበረው 4 ሺህ ሜጋ ዋት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅም አሁን ላይ ወደ 10ሺ ሜጋ ዋት ዕድገት በማስመዝገብ ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የማመንጨት አቅም መገንባቱን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተደረገው ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃም ተቋሙ ከተዘፈቀበት የዕዳ ጫና በማላቀቅ ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገር ማድረጉን አስረድተዋል።

ይህም በተቋማት የፕሮጀክት ግንባታ የገንዘብ በጀት ለታለመለት ዓላማ በማዋል አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን እንደሚያመለክት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ሕዳሴና ገናሌ ዳዋን በውሃ እንዲሁም አይሻና አሰላን በነፋስ ኃይል ማመነጫዎች ለምረቃ ማብቃት መጀመር ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክትን በብቃት የማጠናቀቅ ልምምድ እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።

በዴንማርክ መንግስት የብድርና ድጋፍ በ145 ሚሊዮን ዩሮ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የአሰላ ነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያም በሁለት ዓመታት ውስጥ ዕዳውን መመለስ የሚችል አቅም እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በብድር የምትወስደውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ማዋል ካልተቻለ ለትውልድ ዕዳን ያሸጋግራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የአሰላ ነፋስ ኃይል ጣቢያ በሁለት ዓመታት ዕዳውን የመክፈል አቅምም ለትውልድ ዕዳን ሳይሆን ምንዳን የማስተላልፍ ስኬት ነው ብለዋል።

የዴንማርክ መንግስት ለፕሮጀክቱ ያደረገው የገንዘብ ብድርና ድጋፍም የልማት ትብብር አጋርነት ውጤታማነት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚሹ የልማት አጋሮች የሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።

የአሰላ ነፋስ ኃይል ጣቢያ ግንባታም በአካባቢው የነበረውን የመንገድ መሠረተ ልማት ክፍተትና የእናቶችን ድካም ምላሽ በመስጠት ጭምር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አንስተዋል።


 

ፕሮጀክቱ 100 ሜጋ ዋት ንጹህ የኃይል አቅርቦት በመጨመር ወደ ዘርፈ ብዙ እና ቀጣይነት ባለው የኃይል መጻዒ ዕጣ ፈንታ ለመገንባት የምናደርገውን ጉዞ ያጠናክረዋል ብለዋል።

ይህም የመንገድ መሠረተ ልማቱም የአካባቢው አርሶ አደር ምርታቸውን ለግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ለአፍታም የሚቆም አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ የሚሹ የውስጥና የውጭ ኃይሎችም አይሳካላቸውም ብለዋል።

የተጀመረው የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እናስቀጥላለን፥ ከልማት ውጪ ያለ አካሄድ አዋጭ አይደለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም