ቀጥታ፡

የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ፓርቲዎች የፖለሲ አማራጫቸውን በነጻና በሰላማዊ መንገድ ለህዝቡ እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ወልቂጤ፤ ሚያዚያ 8/2018 (ኢዜአ):-የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት የፖለሲ አማራጫቸውን በነጻና በሰላማዊ መንገድ ለህዝብ ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በጉራጌ ዞን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎች ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የጉራጌ ዞን አስተባባሪ አቶ ደምስ ገብሬ ለኢዜአ እንደገለጹት አሳታፊ ዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ፍትሀዊ ምርጫን ለማድረግ ወሳኝ ነው።  

በጉራጌ ዞን የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም ነፃና ሰላማዊ ምርጫ ለማከናወን የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር   እየሰሩ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

በእስካሁኑ  የምርጫ  ሂደት  የታዩ  ጉድለቶችን ፓርቲዎች  በውይይትና በመነጋገር እየፈቱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የፖለቲካ መህዳሩ መስፋት ፓርታዎቹ ርዕዮተ ዓለማቸውን እና የተለያዩ ፕሮግራማቸውን ለህዝብ በነጻነት ለማስተዋወቅና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለመምከር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዞኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ መንገድን ተከትለው በምርጫው አሸናፊ ለመሆን በነጻነት እየተፎካከሩ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና በብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ናቸው።

ፓርቲያቸው  በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና አሳታፊ  እንዲሆን  የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን  ተናግረዋል።

በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እየተደረገ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም የፓርቲውን የፖሊሲ አማራጮች ለህዝብ ማስተዋወቃቸውን ገልጸዋል።

ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ የጉራጌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አብዱልአዚዝ ሙሰማ (ዶ/ር) በበኩላቸው  በዘንድር ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ ተናግረዋል። 

ይህም እንደፓርቲ ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮች በተለያየ መንገድ ለህዝብ በነጻነት ለማቅረብ እንዳስቻለቸው ገልጸው፣ ፓርቲው የዘንድሮ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለአገር ይጠቅማል ያሉትን ሀሳብ በሰለጠነ መንገድ እያቀረቡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን ባከበረ መንገድ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይበልጥ እንዲጎለብት መሰረት መሆኑን ተረድተው በእዚሁ አግባብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ክርክሩም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና የዜጎችን ክብር ባስጠበቀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም