ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 8/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ በሎጂስቲክስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ፋይዳ ለማሳደግ መሠረታዊ የሆኑት ሎጂስቲክስ፣ ንጹህ ኤነርጂና የሰው ኃይል ክህሎት ላይ ትኩረት መደረጉንም አብራርተዋል።

በተለይም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ማዕከል እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በአየር ላይ ያለውን የትራንስፖርት የበላይነት ከማስቀጠሉም በላይ፣ ለኢንዱስትሪዎች ፈጣን ዝውውር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

ከኃይል አቅርቦት አንጻርም ሀገሪቱ በህዳሴ ግድብ፣ በኮይሻ፣ በሶላር እና በሌሎች የኢነርጂ አማራጮች ምርቶችን ለዓለም ገበያ በርካሽ ዋጋ ለማቅረብ እንደሚያስችላት ነው የተናገሩት።

መንግስት ከኑክሌር ኃይል ለማምረት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ይህም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማኑፋክቸሪንግ መዳረሻ እንደሚያደርጋት ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ ያላትን የወጣት ሀብት ለመጠቀም፣ ወጣቶችን በቴክኖሎጂ የማብቃት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና አማካኝነት ወጣቶች ከኮዲንግና ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር እንዲተዋወቁ መደረጉ፣ ቴክኖሎጂን የሚገነዘብ የተማረ የሰው ኃይል ለመፍጠር እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

ይህ የሰው ኃይል ዝግጅት ለማኑፋክቸሪንግ ማዕከልነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

መንግስት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ ለኤሮስፔስ፣ ለኤሌክትሮኒክስ፣ ለሶላር እና ለኬሚካል ማምረቻ ዘርፎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የግል ዘርፉን ለማገዝ ሲባልም የቦንድ አሠራር እንዲቀርና ብድር ለግሉ ዘርፍ እንዲመቻች መደረጉን፣ ይህም የሀገር ውስጥ ምርታማነትን እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም