ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ የተሳለጠ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማእከላት እየተስፋፉ ነው

ቢሾፍቱ፤ሚያዚያ /8/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ የተሳለጠ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማእከላት እየተስፋፉ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ ተናገሩ።

አስተባባሪው በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግስት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ አገልግሎት የሚዘምንበት እና የፈጠራ ማዕከል እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ከተሞች የንግድ ስፍራ ብቻ ሳይሆን የምርት ማዕከላት በማድረግ ረገድም ውጤታማ የሌማት ትሩፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰው ተኮር ስራዎችን ማዕከል በማድረግ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ተግባራት በውጤታማነት መቀጠላቸውን ጠቅሰው፥ በከተሞች በተለይም የመስሪያ እና የመሸጫ ሼዶች ተገንብተው ለበርካታ ዜጎች ስራ እድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በክልሉ ከተሞች በበጀት ዓመቱ እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት ድረስ ከ11 ሺህ 742 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ለ700 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ማስቻሉን ጠቅሰው፥ ከለውጡ በፊት 10 ሺህ የነበረው የኢንቨስትመንት ቁጥር አሁን ላይ ከ40 ሺህ በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።

ከብድር አቅርቦት አንጻርም ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የተሰጠ ሲሆን ለአጭርና ረጅም ጊዜ በተሰጡ የኢንተርፕረነርሺፕ ስልጠናዎች ከ1 ሺህ 800 በላይ ስራ ፈጣሪዎችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል።

እስካሁን በተለያዩ ከተሞች 17 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች መገንባታቸውንና የኮሪደር ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 115 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 90 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፣ 817 ኪሎ ሜትር የእግር መንገድ፣እና 90 የመኪና ማቆሚያዎች (ፓርኪንግ) እና 40 የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች በክልሉ ከተሞች መገንባታቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም