ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 100 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 100 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መረቁ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8 /2018 (ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ በንፋስ ኃይል አማካኝነት ጨለማን ለመግፈፍ፣ ዐቅምን በለየ የቅድመ ጥናት እና ልዩ እቅድ ወደ ተግባር የተገባበት የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ዛሬ እውን ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ፕሮጀክት 100 ሜጋ ዋት ንጹህ የኃይል አቅርቦት በመጨመር ወደ ዘርፈ ብዙ እና ቀጣይነት ባለው የኃይል መጻዒ ዕጣ ፈንታ ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል።
ይህም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ አብነት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዘመኑ የኃይል ዐቅም ተደማሪ የሆነውን ይህን ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ተገኝተው መመረቃቸውን ጠቁመዋል።
የተገኘው ውጤት መሰል ስራዎችን ለማበራከት የሚያተጋ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በሁሉም ዘርፎች የሚመዘገበው የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ ተጠናክሮ እየቀጠለ ይበልጥ እንደሚለማና ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ታላቅ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።