በካርዳችን ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በካርዳችን ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- ነዋሪዎች
ጎንደር፤ ሚያዚያ 8/2018 (ኢዜአ)፡-በምርጫ ካርዳችን ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ፓርቲን ለመመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ እየተካሔደ መሆኑ ይታወቃል።
ምዝገባው ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን ዜጎች በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት ተመዝግበው ካርዳቸውን በመውሰድ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው እየተገለፀ ነው።
በጎንደር ከተማ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ የነበሩ ዜጎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በመጠቀም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል።
አስተያየት ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሃይለማርያም አለሙ፤ "እኔ አካል ጉዳተኛ ብሆንም ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ሊያመልጠኝ አይገባም በማለት በምርጫው እለት ድምፄን ለመስጠት የሚያስችለኝን ካርድ በእጄ ይዣለሁ" ብለዋል።
በጠቅላላ ምርጫው ለሕዝብ፣ ለሀገርና በተለይም ለአካል ጉዳተኞች ይበጃል ለምለው ፓርቲ ድምፄን ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባት የሆኑት መላዕከ ገነት አባ ገብረመስቀል፤ በህዝብ ድምጽ የተመረጠ መንግስት ለመመስረት ምርጫ ማካሔድ ተገቢ በመሆኑ የመራጭነት ካርድ ወስጃለሁ ነው የሚሉት።
ምርጫ የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫ በመሆኑም ከግጭትና አለመግባባት በመውጣት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገሪቱን የሚያስተዳድሩ አካላትን ወደ ስልጣን ማምጣት ይገባል ነው የሚሉት።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙሃባው ሽፈራው፤ ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በምርጫው ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በሀገር ጉዳይ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይገድበን ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ መስራት ያለብን ሲሆን በመረጥነው መንግስት ለመተዳደር ከወዲሁ የምርጫ ካርድ መያዝ ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጫ ዕለት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።