ቀጥታ፡

የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 8/2018 (ኢዜአ)፦የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነት ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት መገኘቱን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት መመናመን እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የድርቅ መከሰትና ሌሎች አደጋዎች ሳቢያ ህብረተሰቡ ተጎጂ ሆኖ ቆይቷል።

ይህን ታሪክ ለመቀየር መንግሥት በቁርጠኝነት በመስራት፣ግብርናን ማሻገር እንዲሁም ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በተከናወኑ ስራዎች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ከለውጡ መንግሥት ስኬቶች አንዱ የበጋ ስንዴ ልማት መሆኑን ጠቁመው፤ለዘመናት በሚሊዮኖች በሚቆጠር ወጪ ከውጭ ይገባ የነበረው ስንዴ ራስን በመቻል ሀገር ውስጥ ለማምረት ተችሏል ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የድርቅ መከሰትን በዘላቂነት ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በዚህም የተፈጥሮ ሀብት መልሶ እንዲያገግም የሚረዱና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችና እጽዋቶች መተከላቸውን ገልጸው፤ይህም ቀደም ሲል በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚመረቱ ፍራፍሬዎች በሁሉም ቦታ እንዲመረቱ አስችሏል ብለዋል።

በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ የእንስሳት ሀብትን በማልማት በዶሮ፣ ማር፣ ወተት፣ አሳ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፥ በልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ተራቁተው የቆዩ አካባቢዎች አገግመው ወደ ምርታማነታቸው የተመለሱ ሲሆን፤ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችም የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ ያስቻሉ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የደን ልማት፣የአፈር መሸርሸርን የመከላከል ሥራዎች፣ የእንስሳት መኖ አቅርቦትን ማሳደግ እንዲሁም የንብ እርባታ ሥራዎች ላይ በሰፊው እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የውኃ ምንጮችን በመጠቀም በቂ ውኃ ማከማቸት፣ የመስኖ መሰረተ ልማት ማስፋፋት፣ የእንስሳትና የሰብል ልማት ተግባራት ላይም የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል።

በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት"በሚል ኢኒሼቲቭ ከጠባቂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ እንዲዳብር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በ2018 ዓ.ም በሁሉም ክልሎች በሴፍትኔት ሲደገፉ የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

መሰል ውጤታማ ተሞክሮዎችን በማስፋት እንደሀገር ራስን ለመቻል የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚጠናከርም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም