ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም፣ በልማትና በትውልድ ግንባታ ሂደት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው

አሶሳ፤ ሚያዝያ 8/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም፣ በልማትና በትውልድ ግንባታ ሂደት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ምሁር ገለጹ። 

7ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ "ሰላምን ይበልጥ ለማስፋት እና ለማስረጽ የሃይማኖቶች ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር አዳሙ ጅባት (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ የሃይማኖት ተቋማት በተለይም ለትውልድና ለሰላም እሴት ግንባታ የማይተካ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤው መካሄዱ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት በሀገር የሰላም፣ የልማትና የትውልድ ግንባታ ሂደት ይበልጥ ተቀራርበውና ተባብረው መስራት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በዚህ ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ ሀገራዊ ትርጉም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

የኃይማኖት ተቋማት ማኅበረሰባዊ እሴቶችን በመቅረጽ፣ የሞራል መሰረቶችን በማጽናትና የሰላም እሴቶችን በመገንባት ትልቅ አቅም ያላቸው መሆኑንም ተናግረዋል። 

የኃይማኖት ተቋማት በብዝሃነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን አንድ የሚያደርግ ማህበራዊ መስተጋብር የሚያላብሱ መሆኑን አንስተው በቀጣይም የሰላም እና የልማት እሴቶቻቸውን ከዘመናዊ እውቀት ጋር በማቀናጀት ለጋራ ሀገራዊ እድገትና የትውልድ ግንባታ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም