ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ ከሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 8/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፋት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ ከሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው።

መድረኩ “ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትና የተሳለጠ የገበያ ትስስር ለኢኮኖሚ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የተቋሙ ተልዕኮ የመፈጸም አቅሙ በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በዘጠኝ ወራቱ በኦንላይን ንግድ ምዝገባ፣አዲስ ፈቃድ የማውጣት፣ የማደስ እና መሰረዝ ሥራዎች ለሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በወጪ ንግድ ረገድ ከሁሉም የንግድ ዓይነቶች ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል።

የገበያ መሠረተ ልማት በማስፋት ረገድ ገበያ ለማረጋጋት የሚረዱ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 2ሺህ 190 መድረሱን ተናግረዋል።

ሁለተኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላትን የማስፋት ስራ መጠናከሩን አንስተው፤ በዘጠኝ ወራት ሁለት ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ሌሎች ሰባት ማዕከላት በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በምርት ጥራትና ቁጥጥር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልፀው፤ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚመጥኑ ደረጃዎችን የማውጣትና የማስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም