ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጅግጅጋ፣ ሚያዝያ 8/2018(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተተከሉ ችግኞች የአካባቢን ስነምህዳር ከመቀየር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመስጠት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

በሶማሌ ክልል አከባቢ ጥበቃና ገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ የደን ልማት ዳይሬክተር ሂቦ ኑር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በለውጡ ዓመታት በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በተከናወኑት የችግኝ ተከላ ተግባራት መሬት መራቆትና የአፈር መሸርሸርን መከላከል እየተቻለ ነው።

በክልሉ በመርሃ ግብሩ የተተከሉት ችግኞች የአፈር መሸርሸርና የመሬት መራቆት በመከላከልና የአየር ንብረት ተጽዕኖ ለመቋቋም አበረታች ለውጥ ያመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከል ታቅዶ የችግኝ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የታቀደውን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ለማሳካት በ160 የግልና የመንግስት ችግኝ ጣቢያዎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ችግኞቹ ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚሰጡ፣ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዓይነቶች፣ ለደንነት የሚውሉ፣ ለውበትና ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም የሚተከሉ ችግኞችን በመከታተልና አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ የደን ሽፋን ለመጨመር የበኩሉን እንዲወጣ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም