ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የህግ አውጭዎች ትብብር የዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ያጠናክራል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የህግ አውጭዎች ትብብር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከናይጄሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጡ የፓርላማ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ፓርላማ አወቃቀር፣ የስልጣን ዘመንና ተግባሩን በተመለከተ ለናይጄሪያ ፓርላማ ተወካዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቷ ከፍተኛው የህግ አውጭ አካልና አስፈጻሚ አካላትን የሚከታተል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1995 የጸደቀው ህገ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአሀዳዊ አስተዳደር ስርዓት ወደ ፌደራሊዝም እንድትሸጋገር አድርጓታል ብለዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሪፎርም የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ በ13 ቋሚ ኮሚቴ የተቋማት አፈፃፀም ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግበት ገልጸዋል፡፡ 

የህዝብ ተወካዮች ምክርት ቤት 44 በመቶ ሴቶችን የምክር ቤት አባል መሆናቸውን በመግለጽ፤ መንግስት በመከላከያና በሌሎች ተቋማት ሴቶች እንዲመሩ በማድረግ ቁልፍ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ናይጄሪያ የፓርላሜንታዊ ስርዓት የሚከተሉ ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው፤ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የጋራ ዓላማ አላቸው ብለዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ለአፍሪካ ህብረትና ለአህጉሪቱ አንድነት የጎላ አበርክቶ እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ትብብራቸው በመካከላቸው ያለውን ዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በናይጄሪያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊ ጉባኤ አገልግሎት ኮሚሽን አባልና የልዑካን ቡድኑ መሪ ላዋን ማህሙድ፤  ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ብዝሃ ማንነት ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ውይይቱ ዓለም አቀፋዊ የፓርላሜንታዊ ትብብርን ማጠናከር ያስችላል ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ዘላቂነት ያለው ዲሞክራሲ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ፓርላሜንታዊ ስርዓት የሚከተሉና ብዝሃ ማንነት ያላቸው በመሆናቸው ልምዳቸው አንዳቸው ለአንዳቸው ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ነው ብለዋል፡፡


 

ሁለቱ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብት የበለጸጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጋራ ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ ወሳኝ ግንኙነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሰው ሀብት ልማት፣ በቴክኖሎጂ የዕውቀት ብቻ ሳይሆን የክህሎት፣ የሥራ እና ስታርት አፕ ልምዶችን ይለዋወጣሉ ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም