ሃዋሳ ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ነጥብ ተጋሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሃዋሳ ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ነጥብ ተጋሩ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ጨዋታው በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተደርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ ሃዋሳ ከተማ በ42 ነጥብ ደረጃውን ከአራተኛ ወደ ሶስተኛ ከፍ አድርጓል። ቡድኑ ባለፉት አራት የሊጉ ጨዋታዎች ከድል ርቋል። በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ጥሏል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ29 ነጥብ ደረጃውን ከ18ኛ ወደ 17ኛ ከፍ ቢያደርግም አሁንም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ቡድኑ ባለፉት ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን እና ባህር ዳር ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
አማኑኤል ኤርቦ በ41ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ መድን መሪ ሆኗል። አደም አባስ በ96ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፋት ጎል ለባህር ዳር ከተማ አንድ ነጥብ አስገኝቷል።
የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን በ30 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ባህር ዳር ከተማ በ36 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በርካታ ጊዜ (በ15 ጨዋታዎች ) አቻ የወጣ ቡድን ነው።