ይበጀናል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል- የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ይበጀናል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል- የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
ቦንጋ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ):-በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ይበጀናል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት ወር ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲራዘም ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመያዝ የድምፅ መስጫ ቀንን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል መምህር መስፍን ማሞ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን ልማትና ሰላም ያስቀጥላል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርድ እንደወሰዱ ተናግረዋል።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በዜጎች የነቃ ተሳትፎ የሚከናወን በመሆኑ እሳቸውም ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልፀዋል።
የሀገርን ልማትና ሰላም ለማስቀጠል የተሻለ ራዕይ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን እያደረጉት ያለውን ክርክርና የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገርን ለማሻገርና ልማትን ለማጠናከር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያለውን ጥቅም በአግባቡ በመረዳታቸው ከራሳቸው ባለፈ ሌሎችም የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ንጉሴ ገብረሰንበት የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ ናቸው።
በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ይመራኛል፣ መብቴንም ያስጠብቃል፣ የሀገርንና የአካባቢውንም ልማት ያስቀጥላል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት በሂደቱ ላይ በንቃት መሳተፍ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ኬቶ ናቸው።
የምርጫ ሕጉን አክብረው በምርጫው ለመሳተፍ ከመዘጋጀታቸው ባለፈ ሌሎችም የዜጎችን ሕይወት እና ሀገርን የተሻለ ደረጃ ላይ ያደርሳል ላሉት ፓርቲ ድምጻቸውን እንዲሰጡ የማስገንዘብ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት በመሆኑ ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ሁሉ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ በነጻነት በመምረጥ መብቱን ሊጠቀም ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።