ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ግራንድ ፕሪ የሚሳተፉ አትሌቶች በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ ጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7 /2018 (ኢዜአ)፦ የዓለም አትሌቲክስ አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን ውድድር ተሳታፊ አትሌቶች በአዲስ አበባ ስታዲየም ዛሬ ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል። 

የአዲስ አበባ ስታዲየም ከስምንት ዓመት በኋላ የመሮጫ ትራክ እድሳቱ ተጠናቅቆ ዛሬ በአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ ዓለም አቀፍ ውድድር ለሚሳተፉ አትሌቶች ክፍት ሆኗል።

ባለፉት ዓመታት በእድሳት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የነበረው ስታዲየሙ፣ በአዲስ መልክ እድሳት ተደርጎለት አሁን ለውድድርና ለልምምድ ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ቅዳሜ ሚያዚያ 10 የሚደረገውን የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን ውድድር ስኬታማ እንዲሆን፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የመሮጫ መም እድሳቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ላደረገው ርብርብ ፌዴሬሽኑ  ምስጋናውን አቅርቧል።

ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እድገትና ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት ለስፖርቱ መነቃቃት የማይተካ ሚና እንዳለው በመረጃው ላይ ተመላክቷል።

የዓለም አትሌቲክስ ዓመታዊ አህጉራዊ ውድድር አካል የሆነው አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን ውድድር በኢትዮጵያ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም