ቀጥታ፡

በተፈጠረልን የሥራ ዕድል የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ተግተን እየሰራን ነው-የኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች

ደሴ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ከቤተሰብ ጥገኝነት በመላቀቅ ኑሯቸውን ለመቀየርና የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ተግተው እየሰሩ መሆኑን በኮምቦልቻ ከተማ ወደሥራ የገቡ ወጣቶች ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ ሥራና ክህሎት መምሪያ በበኩሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ12 ሺህ 876 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውቋል።

የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት መሀመድ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጸው፣ ቀደም ሲል ሥራ በማጣቱ ምክንያት የቤተሰብ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል።


 

ዘንድሮ በከተማ አስተዳደሩ በተደረገለት የመስሪያ ቦታ ድጋፍ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ከፍቶ የራሱን ሥራ መጀመሩን ገልጾ፣ በዚህም ከቤተሰብ ጥገኝነት በመላቀቅ  ኑሮውን ለማሻሻል ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣት ካሱ ታረቀኝ በበኩሏ በተመቻቸላት የመስሪያ ቦታ በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርታ በምታገኘው ገቢ ከቤተሰብ ጠባቂነት ተላቃ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመረች ተናግራለች።

"ያለሥራ ብዙ የከፋ ጊዜ አሳልፊያለው" የምትለው ወጣቷ ዘንድሮ ባገኘችው የሥራ ዕድል ጠንክራ በመስራት የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስና ሀብት ለማፍራት ግብ ማስቀመጧን ተናግራለች።


 

ለዚህም በሥራዋ ውጤታማ ለመሆን ተግታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሳ፣ ከተማ አስተዳደሩ በመስሪያ ቦታ ያደረገላት ድጋፍ በሥራዋ ውጤታማ እንድትሆን ጠቀሜታ አለው ብላለች።  

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ይትባረክ ጌታሁን በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሮ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግና ዘርፉን ለማነቃቃት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በየደረጃው ያለው አመራር ከዘርፉ ባለሙያ ጋር ተግባብቶ ወደሥራ በመግባቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ12 ሺህ 876 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመለየት ወጣቶች ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸው፣  ከተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች መካከል ግብርና፣ አገልግሎት፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ንግድ፣ ኮንስትራክሽንና ማዕድን እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ሥራ ለመጀመር የገንዘብ እጥረት ላለባቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የተመቻቸ ሲሆን፣ በሥራቸው ስኬታማ እንዲሆኑም የገበያ ትስስር እየተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ግንባታቸው በተጠናቀቁ 12 ሼዶች የተደራጁ ወጣቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸው፣ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትም በሌሎች ዘርፎች የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከአስተዳደሩ ሥራና ክህሎት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም