በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት የአገልግሎት አሰጣጥን ያሻሻሉ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት የአገልግሎት አሰጣጥን ያሻሻሉ ስኬቶች ተመዝግበዋል
ቢሾፍቱ ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳደጉ እና የአገልግሎት አሰጣጥን ያሻሻሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የክልሉ የፓርቲና የመንግሥት የሦስተኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የሀርሰዴ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ ስኬታማ የልማትና የብልጽግና ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይም የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተሻለ መልኩ ያሳደጉ የከተማ እና የገጠር የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ከዚህም ባለፈ የክልሉን የልማት ሥራዎች ለማቀላጠፍ የሚያግዙ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶች መተግበራቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣይም የተመዘገቡ በጎ ሥራዎችን የበለጠ ከማጠናከር ባለፈ፣ ዕቅዶችን በአግባቡ ካለመተግበር ጋር ተያይዘው የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም ይገባል ብለዋል።
በተለይም ሁሉንም የልማት ኃይሎች በማቀናጀት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ውጤታማ ማድረግ ከክልሉ አመራር የሚጠበቅ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በግምገማው ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና በሥራ ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ዝርዝር አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡበትም ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውንና የማኅበረሰቡም ተሳትፎ ጠንካራ እንደነበር ገልጸዋል።
በዘጠኝ ወራቱ በፈተናዎች ውስጥ አልፎ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ኃላፊው፤ በቀረው አጭር የበጀት ዓመቱ ወራት ውስጥ ያልተከናወኑ ሥራዎችን በላቀ ቁርጠኝነት በማከናወን የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመንግስት የማስፈጸም አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት የሚያሳዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።