በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል
ወላይታ ሶዶ ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።
በክልሉ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የበልግ ወቅት ችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር "አረንጓዴ አሻራ ለተምሳሌት ሀገር ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ሼላ ቦርኮሼ ቀበሌ ተካሂዷል።
የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ አመታት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አመርቂ ዉጤት ተገኝቶበታል፡፡
መርሃ ግብሩ የተራቆቱና ከጥቅም ውጭ የነበሩ መሬቶች ለምተው እንደገና ጥቅም እንዲሰጡ ከማድረጉ ባሻገር 18 ነጥብ 95 ከመቶ የነበረውን የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 86 ከመቶ በላይ ለማሳደግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የችግኝ ተከላው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ በመሆኑም ለተያዘው የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላም በቂ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።
በዘርፉ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠልም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በነቂስ ወጥቶ ችግኝ መትከልና መንከባከብ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊና የዲላ ክላስተር አስባባሪ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸዉ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡
በበጋው ወራትም 1 ሺህ 384 የማህበረሰብ ተፋሰስ ውስጥ 159 ሺህ ሄክታር መሬት በዋና ዋና የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ስራዎች መሸፈናቸውም ገልጸዋል።
በበልግ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የጥምር ደን ፣ የፍራፍሬ ፣ የሀገር በቀል እጽዋት፣ የቡና ፣ የእንሰት ፣የጥላና የጌጥ ዛፍ ችግኞች ተከላ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጎድቶ የነበረውን የተፈጥሮ ሀብት መመለስ ተችሏል ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅትም በዞኑ 16 ተራራዎችን ለማልማት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ እንደሆንም አብራርተዋል።