ቀጥታ፡

የሃይማኖቶችን አስተምህሮ ለሰላም እሴት ግንባታ እና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ልንጠቀምበት ይገባል

አሶሳ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የሃይማኖቶችን አስተምህሮ ለሰላም እሴት ግንባታ እና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናገሩ።

7ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ "ሰላምን ይበልጥ ለማስፋት እና ለማስረጽ የሃይማኖቶች ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማጽናት እና የወንድማማችነት ድልድይን ለመገንባት የሃይማኖቶች እኩልነትና አብሮነትን የማጠናከር ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ሃይማኖቶች ለሰላም እና ለህዝቦች አብሮነት ያላቸውን አስተምህሮ በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ሀገራዊ የልማት ስራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የሃይማኖቶችን አስተምህሮ ለሰላም እሴት ግንባታ እና ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል።

የሃይማኖት ካባ ደርበው በህዝቦች መካከል ግጭት ለማስነሳት የሚሞክሩ ግለሰቦችን በማውገዝ የሃይማኖቶችን መቻቻል እና አብሮነትን በሚሰብኩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን ነው ያሉት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በየአካባቢው በመንቀሳቀስ በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት ለማስቀጠልና የሰላምን አስፈላጊነት ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሃይማኖቶች የሰላም እሴት ባለቤት መሆናቸውን የገለፁት አቶ ጌታሁን፤ በሰላም ግንባታ እና በልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክም ሰላምን ይበልጥ ለማስረጽ የሃይማኖቶች ሚና እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እና ሲምፖዚየም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

በመድረኩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ  አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም