ቀጥታ፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ11ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል 

አዳማ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ከዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን ድረስ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2018 የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 250 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 301 ሺህ 160 ሄክታር በማልማት ከዕቅድ በላይ ለማሳካት ተችሏል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ የከርሰ ምድር ውሃ እና የአዋሽ ወንዝን በመጥለፍ የተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የውሃ አማራጮቹን በመጠቀም በዞኑ 11 ወረዳዎች ከለማው መሬት ውስጥ እስካሁን ከ50ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ የስንዴ ሰብል በሰው ጉልበት ታጭዶ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

ከ208 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማው የበጋ መስኖ ስንዴም በኮምባይነር ታግዞ መሰብሰቡን ነው የገለጹት።

የምርት አሰባሰቡን ለማቀላጠፍና የምርት ብክነትን ለመከላከል እንዲቻል 125 ኮምባይነሮች በዞኑ እንዲሰማሩ መደረጉንም አመላክተዋል። 

በእጅና በኮምባይነር ታግዞ በተደረገ የምርት አሰባሰብ ሂደት እስካሁን ድረስ ከ11 ሚሊዮን 104 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መሰብሰቡን አቶ አብነት ተናግረዋል።  


 

እንደ እሳቸው ገለፃ በዞኑ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከተሸፈነው አጠቃላይ መሬት ከ13 ሚሊዮን 100 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ በቅድመ ምርት ትንበያ ወቅት ተገምቷል።

አብዛኛው መሬት በኩታ ገጠም እና በሜካናይዜሽን እርሻ የለማ ሲሆን ይህም ምርትን በፍጥነት ለመሰብሰብና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አውስተዋል።

የመስኖ ልማት ሥራው በዞኑ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚቱን እያሳደገውም ብለዋል።


 

በዞኑ እስካሁን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ285 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በመስኖ ልማት ዘንድሮ በምርታማነት ብልጫ እንዳለ የገለጹት አቶ አብነት፣ ለዚህም ወደ ልማት ያልገቡ ቀበሌዎች በነፍስ ወከፍ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ጭምር ወደ ልማት መግባታቸውን በምክንያትነት ጠቅስዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም