በሐረሪ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጠናከረ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጠናከረ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ሐረር ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆኑን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት አጠቃቀም እና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አራርሶ አደም፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው የችግኝ ዓይነቶች ትኩረት ተሰጥቷል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ከወዲሁ የችግኝ ማፍላትና የተከላ ቦታ መለየትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
በመጪው ክረምት በክልሉ የተራቆቱ አካባቢዎችን ስነ-ምህዳር ለመመለስ የሚያስችሉና የደንነት ጠቀሜታ ካላቸው ችግኞች በተጓዳኝ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ችግኞቹም በመንግስት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችና በግለሰቦች እየተዘጋጁ መሆኑን አንስተው ከእነዚህ ችግኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ቀሪዎቹ ችግኞች ደግሞ ሀገር በቀል ዛፎችና፣ ለእንስሳት መኖና ለደን አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን አቶ አራርሶ አክለዋል።
ጥምር ጥቅም የሚሰጡት የአፕል፣ የማንጎና የአቮካዶ ችግኞችም በክላስተር እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።
በክረምቱ ወራት በክልሉ የሚተከሉት ችግኞች 1ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በስነ ህይወት ለማልበስና መልሶ ለማልማት ግብ መቀመጡን ጠቁመው ለዚህም ከወዲሁ የቦታ መረጣ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ችግኞቹ በተራቆቱ አካባቢዎችንና በማህበረሰቡ ተሳትፎ በ600 ሄክታር መሬት የተፋሰስ ልማት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ቦታ ላይ እንደሚተከሉም አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ክረምት በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር በተራቆቱ አካባቢዎች የተተከሉት ችግኞች በሚደረግላቸው እንክብካቤ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አቶ አራርሶ አክለዋል።