ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራም ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2018 (ኢዜአ)፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራም ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተለወጠ ካለው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር ራሱን እንዲያራምድ፣ ዲፕሎማቶቹም በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራም ይፋ ማድረጊያ መርኃ ግብር አካሂዷል።

ፕሮግራሙ ዲፕሎማቶች ወቅቱ የሚጠይቀውን በቂ እውቀትና ክህሎት ታጥቀው አገራዊ ጥቅምን ለማስከበር እንዲችሉ ለማድረግ የታለመ ነው።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በመርኃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ተቋሙን በላቀ ደረጃ ለማዘመን የሚያስችል የሦስት ዓመት አጠቃላይ የተቋም ግንባታ ፍኖተ ካርታ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል።

የፍኖተ ካርታው አካል የሆኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ተቋሙን የማዘመን  እና ምቹ የሥራ አካባቢን የመፍጠር ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተቋም ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን አቅም ማላቅ ለውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ዲፕሎማቶች ውስብስብ በሆነው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያን በብቃት እንዲወክሉ ክህሎት፣ እውቀትና ግንዛቤያቸው አሁን ካለበት በላይ ከፍ እንዲል እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራሙ ተለዋዋጭ የሆነውን ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ ተቋማዊ አቅምን፣ በውስጣዊ አሠራሩ ዘመናዊ እና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ቀዳሚ ዓላማው እንደሆነ ገልፀዋል።

ዲፕሎማቶች እና የሥራ ኃላፊዎች በሙያዊ ክህሎት፣ በትንታኔ እና በተግባራዊ ዕውቀት እንዲበለጽጉ ማድረግም እንዲሁ።


 

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የዲፕሎማሲ ልምዶችን በተቋሙ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።

የፕሮግራሙ ተግባራዊ መሆን ኢትዮጵያ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንደሚያሳድገው አመልክተው፤ ለሀገሪቷ የዲፕሎማሲ ስኬት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተናግረዋል።

ይህ ሁለገብ የሪፎርም አጀንዳ ለዲፕሎማቶች እና ለሚኒስቴሩ ሠራተኞች የሙያ ሥልጠና መስጠት፣ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት (IFA) ሥርዓተ-ትምህርትን መከለስ፣ አዲስ የሥነ-ምግባር ደንብ ማዘጋጀት እና ከፍተኛ የድህረ-ምረቃ ትምህርቶችን ማመቻቸት የሚሉት ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም