ቀጥታ፡

ተማሪዎች በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እያደረጉ ነው

ደብረ ብርሃን ፤ ሚያዚያ 7 /2018 (ኢዜአ)፦ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  የሚገኙ ተማሪዎች ገለጹ።

በሸዋ ሮቢት አጠቃላይ 2ኛ እና ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሜሮን ሙላቱ ለኢዜአ እንደገለጸችው፤ጊዜዋን በአግባቡ ተጠቅማ በማጥናት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት የሚያስችላትን ውጤት ለማምጣት ጥረት እያደረገች ነው።

መምህራንም ከመደበኛው የትምህርት  ጊዜ  ውጭ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ለፈተናው አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን እንድታደርግ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው የምትናገረው።


 

ትምህርት ቤቱም እንዲሁ አጋዥ መጻህፍትን በማሟላት፣ ቤተ መጻህፍቱን በማደራጀት ፣  የቤተሙከራ  ግብአቶችን በማሟላት ድጋፍ እያደረገ  ነው ብላለች።

በመምህራንና በቤተሰብ የሚደረግላት እገዛ  የተሻለ ውጤት ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ለመቀጠል እየረዳት መሆኑንም ነው ያመለከተችው።

ተማሪ ኑሩ ኢብራሂም በበኩሉ፤ ለሀገር አቀፍ ፈተናው  በቡድንና በተናጠል በማጥናት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ነው ያመለከተው።


 

የትምህርት ቤቱ መምህራን ተማሪዎች ሊኖራቸው ስለሚገባ የአጠናን ስልት፣ በፈተና ጊዜ ሊኖር ስለሚገባ መረጋጋት እና የማናውቀውን ጠይቀን እንድንረዳ የሚያደርጉት ጥረት ዝግጅታችን የተሟላ እንዲሆን እያደረገ ነው ብሏል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አቶ መለሰ ደርብ በበኩላቸው፤  በዞኑ በ54 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 6 ሺህ 219 ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ ተመዝግበዋል።


 

ተማሪዎቹ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዲችሉም አስቀድሞ ከመምህራንና ከወላጅ ህብረት ጋር ውይይት በማድረግ ወደ ስራ መገባቱን ነው ያመለከቱት፡፡

በተለይ ትምህርት ቤቶቹ አጋዥ መጻህፍትን በማሟላት፣ የጥናትና የትርፍ ጊዜ የማጠናከሪያ ትምህርትን  ጨምሮ ሞዴል ፈተናዎችን  በመስጠት ተማሪዎቹ ቀድመው እንዲዘጋጁ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም