ቀጥታ፡

ሃዋሳ ከተማ ከምድረ ገነት ሽሬ መቻል ከድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ዛሬ ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከምድረ ገነት ሽሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ሃዋሳ ከተማ በውድድር ዓመቱ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ በ11ዱ ሲያሸንፍ በሰባቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

30 ግቦችን በ26ቱ ጨዋታዎች ላይ ሲያስቆጥር 21 ጎሎችን አስተናግዷል። ሃዋሳ ከተማ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

በሊጉ ካከናወናቸው 26 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ምድረ ገነት ሽሬ በበኩሉ 10 ጊዜ ተሸንፏል። 10 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 17 ግቦችን ሲያገባ 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ምድረ ገነት ሽሬ በ28 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሃዋሳ ከተማ ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የሚያስችለውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል። ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደርጋል። 

ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ ያልቻለው ምድረ ገነት ሽሬ ሶስት ነጥብ ማግኘት ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ወሳኝ የሚባል ነው። 

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቶ ከሚያዚያ 5 ወደ ዛሬ የተሸጋገረ ነው። 

በሌላኛው መርሐ ግብር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከመቻል በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። 11 ጊዜ አቻ ተለያይቷል።  18 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 25 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ32 ነጥብ 14ተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ በውድድር ዓመቱ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ በ10ሩ ድል ሲቀናው ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች  አቻ ወጥቷል። 33 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 21 ግቦች ተቆጥረውበታል። 

መቻል በ40 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  

በ26ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ምድረ ገነት ሽሬን 1 ለ 0፣ መቻል የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡናን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በድል ጉዟቸው ለመቀጠል ይፋለማሉ። 

በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባካሄዳቸው 26 ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። በ11 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 20 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ 20 ጎሎች ተቆጥረውበታል። መድን በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ ከ26 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አጋጥሞታል። በ14 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 19 ግቦች ሲያስቆጥር 18 ግቦችን አስተናግዷል።

ባህር ዳር ከተማ በ35 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ስጋት በመጠኑ እንዲርቅ ያስችለዋል።

በ26ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን 2 ለ 1 የረታው ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በርካታ ጊዜ (በ14 ጨዋታዎች ) አቻ የወጣ ቡድን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም