በድሬዳዋ አስተዳደር ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 7/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የፍራፍሬ እና ለደንነት የሚውሉ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የአስተዳደሩ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዓመታት በአስተዳደሩ የተተከሉ ችግኞች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የገጠሩን ማህበረሰብ ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገሩ መሆናቸውም ተመላክቷል።
በድሬደዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በአስተዳደሩ በሚገኙ ከ20 በላይ የችግኝ ጣቢያዎች የተለያዩ ችግኞች በጥራት እየተዘጋጁ ነው።
ከአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ የፍራፍሬ፣ የደንና የውበት ችግኞች በማፍላት ለተከላ ዝግጁ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
በዘንድሮ ክረምት ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ከድሬደዋ ስነምህዳርና አየር ንብረት ጋር ስምሙ የሆኑ የተለያዩ ፍራፍሬዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
የሚተከሉት ፍራፍሬዎች በተለይም የገጠሩን ማህበረሰብ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገርና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እያገዙ መሆናቸውን በማስገንዘብ።
አቶ ማስረሻ አክለውም ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በአስተዳደሩ የተተከሉት ችግኞች ከ80 በመቶ በላይ ፀድቀው የግብርናን ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ምቹ መደላድል ከመፍጠር በዘለለ የሌማት ትሩፋት መርሃግብርን ውጤታማ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
በባለስልጣኑ የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሰባት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተተከሉት ችግኞች የድሬዳዋን በረሃማ ስነምህዳር በመቀየር የከተማዋን የጎርፍ ተጋላጭነት እያስቀሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም በገጠር ቀበሌዎች የተተከሉት የሎሚ፣ የፓፓያ፣ የብርትኳን እና ሌሎች ምርጥ የፍራፍሬ ችግኞች የአርሶአደሩን ገቢ በመጨመር እና ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኙ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ፍሬያማ ውጤቶች ለማስቀጠል በአሁን ሰዓት እየጣለ የሚገኘውን የበልግ ዝናብ ጥቅም ላይ በማዋል 75 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞች በገጠር ቀበሌዎች መተከላቸውን ለአብነት አንስተዋል።
እንደ አቶ ማሙሽ ገለፃ ባለፈው ጥር ወር የተካሄደው የተፋሰስ ልማት በአስተዳደሩ ለሚተከሉት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የጉድጓድ ቁፋሮ እና ሌሎች ዝግጅቶች በከፊል እንዲጠናቀቁ አስችሏል።
እነዚህ የቅድመ ተከላ ዝግጅቶች የመጪውን ክረምት የችግኝ ተከላ በላቀ እና በተናበበ መንገድ ዳር ለማድረስ እንደሚያስችሉም አንስተዋል።
በአስተዳደሩ ባለፉት ሰባት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻዎች ህብረተሰቡንና ባለድርሻዎችን በማስተባበር የተለያዩ የደን፣ የውበት እና የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለው የድሬደዋን የደንና ስነምህዳር በከፍተኛ ደረጃ እየለወጡ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።