የከተማ እና ከተሜነት እሳቤ ለሀገር ግንባታ መሰረት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ እና ከተሜነት እሳቤ ለሀገር ግንባታ መሰረት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የከተማ እና ከተሜነት እሳቤ ለሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚና እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
“የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው የከተማ እና የከተሜነት እሳቤ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ስኬት ያለውን ወሳኝ ሚና አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም የሀገረ መንግስት ግንባታ ሊከናወንና ሊሳካ የሚችለው በጥግግት የሚኖሩ ሰዎች ሲኖሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በጥግግት የሚኖር ማህበረሰብ ለኢኖቬሽን እና ለውድድር እጅግ ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።
የሕዝብ ጥግግት ለልማት እጅግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ልማትንና ብልጽግናን የሚያስብ ማንኛውም መንግስት ከተማን፣ ከተሜነትን፣ ግብር መክፈልንና አገልግሎት መስጠትን ማዕከሉ ካላደረገ ልማት ሊያመጣ እንደማይችል አስገንዝበዋል።
ከተማ አያስፈልግኝም፣ የእኔ ትኩረት አርሶ አደር ብቻ ነው የሚል እሳቤ ካለ ልማትን ማሰብ እንደማይቻልም አክለው ገልጸዋል።
በጥግግት የሚኖር ማህበረሰብ የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛና የነቃ መሆኑን ገልጸው ማህበረሰቡ ግብር የሚከፍልና ለመሠረተ ልማት ቅርብ በመሆኑ የሚነገረውን በቅርበት እንደሚሰማም አስረድተዋል።
መንግስት ከትናንትናው ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን በመውሰድ ቀጣይነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ስራዎች እየታረሙና እየታረቁ በመሄዳቸውም በአሁኑ ወቅት አመርቂ ውጤት እየመጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።