የባየር ሙኒክ እና የሪያል ማድሪድ ተጠባቂ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የባየር ሙኒክ እና የሪያል ማድሪድ ተጠባቂ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቀሪ ሁለት የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን ይካሄዳሉ።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ባየር ሙኒክ ከሪያል ማድሪድ 75 ሺህ 24 ተመልካቾችን በሚያስተናግደው አሊያንዝ አሬና ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት በበርናባው ባካሄዱት ጨዋታ ባየር ሙኒክ 2 ለ 1 አሸንፏል።
ሉዊስ ዲያዝ እና ሃሪ ኬን የማሸነፊያ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ኪሊያን ምባፔ ለማድሪድ ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱ ባየር ሙኒክ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ያለውን እድል የተሻለ አድርጓል።
የ15 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ሪያል ማድሪድ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የመግባት እድሉ ያበቃለት አይደለም።
በሻምፒዮንስ ሊጉ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ማድሪድ ውጤቱን ለመቀልበስ ጠንካራውን ባየር ሙኒክ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
የስድስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ባየር ሙኒክ፣ ወደ ግማሽ ፍፃሜው (አራት ውስጥ) የመግባት ዕድሉ በራሱ እጅ ላይ ይገኛል።
በሌላኛው መርሐ ግብር አርሰናል ስፖርቲንግ ሊዝበንን ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ያስተናግዳል።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል ከሜዳው ውጪ በካይ ሃቫርትዝ ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል።
አርሰናል ወደ ግማሽ ፍጻሜ የመግባት ሰፊ ግምት አግኝቷል።
የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ በውድድሩ ጠንካራ ቡድን የሆነውን አርሰናልን ከሜዳው ውጪ የማሸነፍ ከባድ የቤት ስራ ይጠብቀዋል።
ትናንት በተደረጉ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ፒኤስጂ ሊቨርፑልን፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ባርሴሎናን በድምር ውጤት በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።