ቀጥታ፡

ፒኤስጂ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ለግማሽ ፍጻሜ አለፉ

አዲስን አበባ፤  ሚያዝያ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ማምሻውን ተደርገዋል።

በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፒኤስጂ ሊቨርፑልን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ኡስማን ዴምቤሌ በ72ኛው እና 91ኛው ደቂቃ  የማሸነፊያውን ጎሎቹን አስቆጥሯል።

 

የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ በድምር ውጤት 4 ለ 0 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል።

ፒኤስጂ በግማሽ ፍጻሜው ከባየር ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ 1 አሸንፏል።

 

በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ላሚን ያማል እና ፌራን ቶሬስ ለባርሴሎና ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

አዴሞላ ሉክማን ለአትሌቲኮ ማድሪድ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

የባርሴሎናው ኤሪክ ጋርሺያ በ80ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

በመጀመሪያው ጨዋታም የባርሴሎናው ፓው ኩባርሲ በቀይ ካርድ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

 

በጨዋታው ባርሴሎና ብልጫ ቢወስድም ጨዋታውን ለመቀልበስ የሚያስችሉ ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር አልቻለም።

ውጤቱን ተከትሎ አትሌቲኮ ማድሪድ በድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

የማድሪዱ ክለብ በግማሽ ፍጻሜው ከአርሰናል እና ስፖርቲንግ ሊዝበን አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ነገም ሲቀጥል ባየር ሙኒክ ከሪያል ማድሪድ እና አርሰናል ከስፖርቲንግ ሊዝበን ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም