ቀጥታ፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፦የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የትምህርትና ክህሎት ለሥራ (ኢዝ) ፕሮጀክት አስተባባሪ ገለጹ።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የትምህርትና ክህሎት ለሥራ (ኢዝ) ፕሮጀክት ለ12 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሥራና ክህሎት ቢሮዎች የአይ ሲ ቲ መሰረተ ልማት ድጋፎች አድርጓል።


 

ሚኒስቴሩ ድጋፍ ካደረጋቸው መካከል ኮምፒውተሮች፣ የኔትወርክ መሰረተ ልማት ቁሳቁሶች፣ ለቪዲዮ ኮንፍረንስ የሚያገለግሉ ቴሌቪዥኖች፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጄኔሬተሮችና የሶላር ፓኔሎች ይገኙበታል።    

በሚኒስቴሩ የኢዝ ፕሮጀክት አስተባባሪና የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሀፍቶም ገብረእግዚአብሄር እንዳሉት፤ የሥልጠና ማዕከላትን በዘመናዊ መንገድ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የመሰረተ ልማት ማሟላት ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።   

ለአብነትም ሚኒስቴሩ ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር 70 ኮሌጆች አስፈላጊው መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው መደረጉን ጠቁመው፤ በዚህም የሥልጠና አቅምን ከፍ ያደረጉ ውጤቶች እየተገኘበት ነው ብለዋል። 

ዛሬ ፕሮጀክቱ ለ12ቱ ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ ያደረገው የአይ ሲ ቲ መሰረተ ልማቶች ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም አክለዋል።  

ድጋፉ እንደ ሀገር ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብርን ስኬታማ ከማድረግ አኳያ ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል።   

የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዳግማዊት ግርማ፤ ወጣቱ የዲጂታል ክህሎት አዳብሮ የርቀት ሥራዎች (ሪሞት ጆብስን) ጨምሮ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል።  


 

የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች መገኘታቸው ለሥራው መቃናት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።  

የኦሮሚያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ነስረዲን ቃዲ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከመደበኛ ስልጠና ባሻገር የነዋሪዎችን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ሕዝባዊ ስልጠና መርሃ ግብር ተጀምሯል ብለዋል።


 

ዛሬ የተገኘው ድጋፍ ሥራውን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም  ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።  


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዓለሙ ገብሬ እንደገለጹት፤ ድጋፉ በክልሉ የሚገኙ የሥልጠና ማዕከላት ሥልጠናዎችን በጥራትና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ እንዲያደርጉ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም