ቀጥታ፡

ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አይተኬ ሚና አለው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡- ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ፣ የተሻገረ ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ በበቂ ሁኔታ ዜጎችን ሥራ ለማስያዝ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሚና አይተኬ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚሁ ወቅትም፤ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን አንዳንዶች የዕድገት ሞተር እንደሚሉት አንስተዋል።

የዕድገት ሞተር የሚያስብለው ዋናው ምክንያትም፤ ምርታማነትን (ፕሮዳክቲቪቲን) በማሳደግ ረገድ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ያለው ሚና ከሌሎች ሴክተሮች ጋር የሚወዳደር ስላልሆነ ነው ብለዋል።

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ወጭ ንግድ (ኤክስፖርት) መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ ለኤክስፖርት ብዛትም ጥራትም ወሳኝ መሆናቸውን በማስገንዘብ፤ ብዙ አምርተን፣ በቂ ተጠቅመን ስናበቃ ነው ምንሸጠው ብለዋል።

በዚህ ሂደትም ደረጃውን ለጠበቀ ምርት መስፋፋት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ሚና አለው፤ ለምርታማነትም ለኤክስፖርትም የዕድገት ሞተር ሆኖ ይወሰዳል ሲሉ አብራርተዋል።

ሌላኛው ቁልፍ ምክንያት ደግሞ፤ መዋቅራዊ ሽግግር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ አንድን የኢኮኖሚ ዘውግ ወደሚቀጥለው የኢኮኖሚ ዘውግ ለመውሰድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አይተኬ ሚና አለው ሲሉም በአጽንኦት አንስተዋል።

ኢንዱስትሪን የማይጠቀሙ የኢኮኖሚ ዘውጎች ጥሬ ዕቃ አቅራቢ ሊሆኑ ይችላሉ፤ የጥሬ ዕቃ አቅራቢ የሚያደርገው ጉዳይ ፕሮሰስ የማድረግ ዐቅም (ካፓሲቲ) ካልተፈጠረ ነው በማለትም አስረድተዋል።

ስለዚህ ከጥሬ ዕቃ ወደ ፕሮሰስ የተሻገረ ዕቃ ለማምጣትም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው ያስረዱት።

ሌላኛው የማኑፋክቸሪንግ ቁልፍ ጉዳይ ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፈጠራን (ቴክኖሎጂን) የሚያመጣው ለራሱ ብቻ አለመሆኑን ገልጸው፤ ለሌሎች ዘርፎችም መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ያለውን ሚና ገልጸው፤ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከሌሎች ሴክተሮች ጋር እንደማይነጻጸር ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሥራ ይፈጥራል፣ ኢኮኖሚ ያሸጋግራል፣ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሻገር እንደ መስፈንጠሪያ ሆኖ ያገለግላል በማለት አብራርተዋል።

በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት አንዱ አንጓ ነው፤ አጀንዳ ነው በማለት በአጽንኦት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም