ቀጥታ፡

በፈተናዎች ሁሉ የጸናው የኢትዮጵያና የላይቤሪያ ወዳጅነት

በሙሴ መለሰ

ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት አላቸው። ይሄ ወዳጅነት በፈተናዎች ጊዜ ሁሉ ጸንቶ የዘለቀም ነው።

ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ውስጥ ብቸኛ ነፃ ሀገራት በመሆናቸው፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች (ለምሳሌ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ) የአፍሪካውያን ድምፅ ሆነው በጋራ ይቆሙም ነበር።

የሀገራቱ የወዳጅነት እና የትብብር ስምምነትም እ.አ.አ በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ የጀመረ ሲሆን፣ በመካከላቸው ያለው ዘላቂ ወዳጅነት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች (እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) በጋራ ለመቆም ቃል የተገባበት ሰነድም ተደርጎ ይወሰዳል።

የዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረት የጣሉትም ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እና ፕሬዝዳንት ዊሊያም ቱብማን ናቸው።

እ.ኤ.አ. በ1954 ፕሬዝዳንት ቱብማን ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ይፋዊ ግንኙነት እንዲጀመር በር ከፍቷል።  ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ  እ.አ.አ. 1958 ጉብኝት ወደ ሞንሮቪያ በማድረግ፣ በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ የነፃነት ንቅናቄዎችን በጋራ ለመደገፍ ተወያይተዋል።

እነዚህ ጉብኝቶች የሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆኑ አህጉራዊ ፋይዳም ነበራቸው። እ.አ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ሲመሰረት፣ ሁለቱ ሀገራት "የሞንሮቪያ" እና "የካዛብላንካ" ቡድኖችን ልዩነት በውይይት በመፍታት ለአህጉሪቱ አንድነት የጀርባ አጥንት መሆናቸውን አስመስክረዋል።

በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በ”ሞንሮቪያ ቡድን” እና "የካዛብላንካ ቡድን" መካከል የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በጋራ በመስራታቸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊመሰረት ችሏል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በችግር ውስጥ የተፈተነ ወዳጅነት ነው የሚል ሀሳብ በብዙዎች ይነሳል። የዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በላይቤሪያ የነበራት የሰላም ማስከበር ሚና ነው።

ላይቤሪያ 14 ዓመታት በዘለቀው አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት መንግሥታዊ መዋቅሯ ፈርሶ ነበር።

... 2003 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) ሰላም እንዲያስከብሩ ከጠራቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ነበረች።

ኢትዮጵያ በላይቤሪያ በርካታ ሰራዊቷን በማሰማራት ለሀገሪቷ ሰላም ዋጋ ከፍላለች።

ሰራዊቱ አማፂያንን ትጥቅ በማስፈታት፣ ተዋጊዎች ከማህበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ በማድረግ እና የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል።

ዋና ከተማዋ ሞንሮቪያ እና በገጠራማ አካባቢዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዳይጣስ ጥብቅ ቁጥጥር አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት የጤና ቡድን በየሰፈሩ በመዘዋወር ለላይቤሪያውያን ነፃ የህክምና እርዳታ እና መድሃኒትም ይሰጥ ነበር።

ሰራዊቱ የራሱን ስንቅ ለተቸሩ ዜጎች በማካፈል ወንድማማችነትን በተግባር አሳይቷል።

እ.ኤ.አ በ2014 የኢቦላ ወረርሽኝ በላይቤሪያ በከፋ ሁኔታ በተከሰተበት ወቅትም፣ ሌሎች ሀገራት ሰራዊታቸውን ሲያስወጡ ኢትዮጵያ ግን የህክምና ቡድኖችን እና ሰራዊቷን በማቆየት ከላይቤሪያ ህዝብ ጎን ቆማች።

ኢትዮጵያ በላይቤሪያ ሶስት ተከታታይ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች እንዲካሄዱ በሰላም ማስከበሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የላይቤሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች የላቀ አገልግሎት ሜዳሊያ እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በላይቤሪያ የነበራት የሰላም ማስከበር ሚና ከወታደራዊ ተልዕኮ ባለፈ የደም እና የአጥንት መስዋዕትነት ከፍላለች። ይህ የሰራዊቱ ተሳትፎ ዛሬም ድረስ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ላለው ጥብቅ ወዳጅነት ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ ይወሳል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራቱ መካከል የሚደረጉ የጉብኝት ልውውጦች እና ውይይቶች ለሁለትዮሽ ትብብሩ መጠናከር አስተዋጽኦ አድርገዋል።

የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እ.አ.አ በ2006 ስልጣን በያዙ ማግስት አዲስ አበባን ጎብኝተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በላይቤሪያ ሰላም ለማስፈን ላደረገችው ድጋፍ እውቅና የሰጡበት ነበር።

ሰርሊፍ በላይቤሪያ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ሲያበቃ እ.አ.አ ጁላይ 2015 ኢትዮጵያን በመጎብኘት ለተደረገላቸው የህክምና ቡድን ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት እ.አ.አ በ2017 ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳላኝ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቷ በወቅቱ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን የጎበኙ ሲሆን ላይቤሪያ ከኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ልማት ዘርፍ ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

የላይቤሪያ የእግር ኳስ ኮከብ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ እ.አ.አ በ2018 ስልጣን ከያዙ በኋላ በአዲስ አበባ በተካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ ተወያይተዋል።

የቀድሞው የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲ-ማክስዌል ሳህ ከማያህ እ.አ.አ በ2022 በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን (Joint Ministerial Commission) እንዲቋቋም ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በላይቤሪያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (UNMIL) ላይ በነበረበት ወቅት፣ የተለያዩ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና የጦር አዛዦች የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመጎብኘት እና ከላይቤሪያ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት በተደጋጋሚ ወደ ሞንሮቪያ ተጉዘዋል።

ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ውይይቶች በተለያዩ ዘርፎች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶችም ተፈራርመዋል።

ሰላም ፣ ደህንነት፣ ጤና፣ የአየር አገልግሎት፣ የቪዛ ነፃ መብት ፣ የንግድ ትብብር ማዕቀፍ፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ባህል እና ስፖርት ስምምነት ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የአየር አገልግሎት ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞንሮቪያ ያለምንም ገደብ እንዲበር እና ላይቤሪያን ከቀሪው ዓለም ጋር ማገናኘት የሚያስችል ህጋዊ ማዕቀፍ ነው።

የሰላም ማስከበር ስምምነቱ በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንድትልክ የተደረገው ስምምነት በላይቤሪያ መረጋጋት እንዲመጣ ትልቅ ድርሻ ነበረው።

በኪነ-ጥበብ እና በስፖርት ዘርፍ (በተለይም በእግር ኳስ) የሁለቱ ሀገራት ወጣቶች ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል።

የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦአከይ እ.አ.አ 2023 ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡበት ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ለማደስ እና በንግድ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካቲት ወር 2018 ዓ.ም ከተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦአካይ ጋር ውይይት አድርገዋል።

የሁለትዮሽ ውይይቱ በቴክኖሎጂ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ኢትዮጵያ ለመገንባት ባቀደችው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያተኮረ ነበር።

በውይይቶቹ ላይ ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ ለስራ ጉብኝት ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ የነገ ብሩህ ተስፋ እየተሰራባት ወደ ምትገኘው ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ እንኳን በሰላም መጡ ብለዋል።

በፕሬዝዳንቱ ቆይታ እጅግ ፍሬያማ ውይይት እንደሚኖራቸውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የፕሬዝዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ የስራ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት የበለጠ እንደሚያጠናክርም ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ እና የላይቤሪያ መጻኢ ግንኙነት ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ አጋርነት የማሳደግ ፍላጎት በሁለቱም ወገን በኩል አለ።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የአቪዬሽን ትስስር፣ የቴክኖሎጂ ልውውጥ እና በአህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ማዕቀፍ የሚደረግ ትብብር ለጋራ ብልጽግና መሰረት ይጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም