በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ያገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ያገኛሉ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018 (ኢዜአ)፡-በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ለበልግ ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እንደሚጠናከር አስታውቋል።
በዚህም በልግ ዋነኛና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት የደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች፣ ስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች፣ መካከለኛው፣ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎችም እንዲሁ።
የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ጨምሮ ሰሜን ምዕራብና የምዕራብ የሀገሪቱ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።
በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚ.ሜ በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
በሚያዚያ የመጀመሪያዉ አስር ቀናት ከሚኖረው ከፍተኛ የፀሐይ ሀይል ጋር በተያያዘ በተለይም በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ3 እስከ 41 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚሆንም ተመላክቷል።
በመደበኛ ሁኔታ የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ በልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ እስከ ሚያዚያ የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት ቀጣይነት የሚኖረው ሲሆን በተጨማሪም ከሚጠናከሩት ሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ጋር ተያይዞ ወቅታዊው ዝናብ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ እንደሚስፋፋ ተገልጿል።
በሚያዚያ የመጪዎቹ አሥር ቀናት በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ቀጣይነት እንደሚኖረው የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ ገጽታ እንደሚኖራቸው ትንበያው አመላክቷል።
በመሆኑም በልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።
በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገራችን አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል።
ዋነኛ እና ሁለተኛ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚና የበልግ ሰብል አብቃይ በሆኑት የደቡብ ኢትዮጵያ፤ የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች የስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎችና የመካከለኛው የሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የተስፋፋ እርጥበት እንደሚያገኙ ተመላክቷል።
እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ሰሜን ምዕራብ እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተስፋፋ እርጥበት ያገኛሉ ተብሏል።
በመሆኑም አርሶ አደሮች አርብቶ አደሮች እና የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቁ መልካም ሁኔታዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።
እንዲሁም ሊኖር የሚችሉ ተያያዥ ስጋቶችን ለመቀነስ የተቀመጡትን ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩት አስገንዝቧል።