የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ የኮሜሳ አባል ሀገራት ያላቸውን የጋራ ትብብር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ የኮሜሳ አባል ሀገራት ያላቸውን የጋራ ትብብር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 6/2018(ኢዜአ)፡-የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ የኮሜሳ አባል ሀገራት ያላቸውን የጋራ ትብብር ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን ጥሪ አቀረቡ።
በስርዓተ ጾታ እኩልነትና የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው 15ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴክሬታሪያት የቴክኒካል ኮሚቴ አህጉራዊ ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ተቀርፆ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በዚህም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ዘርፎች በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ሴቶች በንግድ ዘርፍ ላይ በሚፈለገው ደረጃ ሰርተው መለወጥ እንዳይችሉ ማነቆ ከሆኑ ተግዳሮቶች መካከል የፋይናንስ እና የመሥሪያ ቦታ ችግር ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህን ለመፍታት መንግስት የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካውያን ሴቶችን በንግድ ስርዓቱ ላይ ተሳታፊና እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ሴቶች በንግድ ላይ ለመሳተፍ ማነቆ የሆኑባቸውን ተግዳሮት በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የኮሜሳ አባል ሀገራት ተቀራርበን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የኮሜሳ አባል ሀገራት ያላቸውን ቅንጅታዊ ስራ በይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ረዳት ፀሀፊ አምባሳደር ማህመድ ካዳ በበኩላቸው፤ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ልማትን ከማሳለጥ ባለፈ አሁጉራዊ ትስስርን የበለጠ ለማጠናከር ያስችላል።
ኮሜሳ ሴቶች በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያላቸውን የስርአተ ጾታ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚወጡ አሰራሮችን ለመደገፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ሴቶች የፋይናንስ፣ የዲጂታል ክህሎት፣ የገበያ፣ የውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በኮሜሳ ሴክረተሪያት ሲኒየር ጀንደር ሜንስትሪሚንግ ኦፊሰር አንደር ጀንደር ኤንድ ሶሻል አፊር ሴክሬታሪያት ፅጌ ታደለ በበኩላቸው፤ በኮሜሳ አባል ሀገራት ላይ ሴቶችና ወጣቶች በኢኮኖሚያዊ ተግባራት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማጎልበት ፍትሀዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።